አለ ልባል ብቻ አልኖርም
አለህ አንተ እኮ እንዲህ ነህ ተብዬ
ለመከበር ለመሞካሸት ብዬ
አልኖርም
ራሴን እየደለልሁ ወገኔን አላታልም
ሥራዬ ካልተናገረ
ተግባሬ ካልመሰከረ
ድርጊቴ እኔን ካላስከበረ
አለ እየተባልኩ ሳልኖር
ጠቢብ ስባል ሳልማር
በከንቱ ውዳሴ ስቆለጳጰስ ከምኖር
ስጋዬ ይበስብስ ልሙት በቃ ልረሳ
ስሜ ብቻ በሰራሁት መልካም ይነሳ
በዚህች ከንቱ ዓለም
በሸር ተንኮል ከምፍገመገም
ጥንቅር ብዬ ልቅር ልጥፋ
ለባዘነው ወገኔ ካልሆንኩ ተስፋ
መኖሬ ካልሆነ ለሌላው ቤዛ
ለተራበ ለተጠማው መንፈሴ ካልተገዛ
ያቅሜን ካላደረግሁ
የምችለውን ካልሰጠሁ
በእሾህ ጋሬጣ እየተወጋ
ቀን ከሌሊት እየፈጋ
ሳይኖረው ለሰጠኝ
ሳይደላው እዚህ ላደረሰኝ
ህሊናዬ ምን መልስ አለው
ምን ብዬ በምን ውስጤን ልደልለው
የኔ መኖር ትርጉም የለው
ከራሴ ጋር ስዋጋ ከምኖር
ልሙት በቃ ልቀበር
ነጭ ለብሼ ስወደስ ተከሽኜ
ያላደረግሁትን ያልሆንሁትን ሆኜ
ከምውገረገር
ከመሸበት ልደር
እውነት ተናግሬ
ለቀናነት መስክሬ
ደካማ ወገኔ ጋር አብሬ
ያለኝን አካፍዬ
ክስት ሆኖ ሥራዬ
ማንነቴ ይገለጽ እኔነቴ ይታወቅ
ምግባሬ ይቃና ሥርዓቴም ይታረቅ
አለ ልባል ብቻ አልኖርም
ባልሰራሁት አልከብርም
ባልሁንኩት አልወደስም
መኖሬ ምክኒያት ይኑረው
እኔን እኔ እንድወደው።
ከአሻግረው
No comments:
Post a Comment